ሀገራችን ኢትዮጵያ በታላቁ 32ኛው የቶክዮ 2020 ኦሊምፒያድ በመሳተፍ ህዝባችን የሚጠብቀውን እና የተለመደውን ውጤታማነት ለማስመዝገብ ብሎም በኩነቱ የሀገራችንን መልካም ገጽታ ግንባታ ለማጠናከር ለዝግጅቱና ለተሳትፎው የቀራት ከሶስት አመታት ያነሰ ጊዜ ብቻ ነው፡፡

ስለሆነም የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ አዲሱ አመራር እና የኮሚቴው ሠራተኞች የቀድሞውን አመራር የስራ ትሩፋቶች እና ትልሞች የማስቀጠሉ ስራ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ኮሚቴው ራሱን አሁን ካለው አለም አቀፍ የኦሊምፒክ እንቅስቃሴ ነባራዊ ሁኔታ ጋር በማጣጣም ብሎም በስትራቴጂካዊ አስተሳሰብ ቅኝት በመመራት የራሱን ፍኖተ ካርታ (ስትራቴጂክ መስመር) በመቅረጽ ለስኬታማነት መጓዝ ከጀመረ ቀናቶች መቆጠር ጀምረዋል፡፡

ያለ ቅንጅታዊ ስራ ውጤታማነት ህልም እንጂ እውን እንደማይሆን የተገነዘበው የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ መላውን የኦሊምፒክ ቤተሰብ ያሳተፈ የአራት አመት ስትራቴጂክ ዕቅድ ቀርጾ ግቡን ሊመታ በከፍተኛ የስራ ተነሳሽነት እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡

በዚህ አግባብ ኮሚቴው ወደ ታላቁ የቶክዮ 2020 ኦሊምፒክ ጨዋታዎች የሚያዳርሰውን በርካታ ወሳኝና መደላድል የሆኑ ተግባራትን ማከናወን ጀምሯል፡፡ ኮሚቴው ከፍተኛ የሆነ የህዝብ ንቅናቄ በመፍጠርና በማቀጣጠል የሀገራችንን ህብረተሰብ ከወትሮ በተለየ ከጎኑ በማሰለፍ ለውጤታማነት ግስጋሴ ይተጋል፡፡

ስለሆነም የኦሊምፒክ ፍልስፍና እና ኦሊምፒዝምን በሀገራችን የማስፋፋት ስራ ከመከወን ጎን ለጎን በርካታ የስፖርት ልማቶች ይከናወናሉ፡፡ አቅም በፈቀደ አግባብ ለሀገር አቀፍ የስፖርት ማህበራት፣ በተለይ ለስፖርታችን ወሳኝ ተዋንያን አካላት አትሌቶቻችን፣ አሠልጣኞችችን እና የስፖርት አመራሮቻችን ላይ በዋንኛነት የስፖርት ልማት ስራዎች (የአቅም ግንባታ ስራዎች) ይከናወናሉ፡፡ የኦሊምፒክ መሰረተ ልማት ጅምር ግንባታዎችም እንዲጠናቀቁ እና አገልግሎት ላይ እንዲውሉ ከፍተኛ ጥረት ይደረጋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ከስፖርታዊ ኩነቶች አኳያ የቶኪዮ 2020 የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ከመድረሱ ቀደም ብሎ በሀገር፣ በአህጉር እና በአለም አቀፍ ውድድሮች በምንሳተፍባቸው ማለትም በ6ኛው የመላ ኢትዮጵያ፣ በ12ኛ የመላ አፍሪካ፣ በ3ኛው የአፍሪካ የወጣቶች ኦሊምፒክ፣ እንዲሁም በ3ኛው የአለም ወጣቶች ኦሊምፒክ ጨዋታዎች በመሳተፍ አመርቂ ውጤት ለማምጣት የምንሰራው ቅንጅታዊ ስራ እንደተጠበቀ ሆኖ በሁለቱም ጾታዎች ሀገራችንን የሚያስጠሩ በረካታ ጥራትና ብዛት ያላቸው ተተኪ አትሌቶችንን እናፈራለን፡፡

በመጨረሻም በዚህ አጋጣሚ ለኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ታላቅ ትልሞች ስኬታማነት የሁሉም የኦሊምፒክ ቤተሰብ ድጋፍ ከጎናችን እንዳይለየን በአክብሮት እጠይቃለሁ፡፡ አመሠግናለሁ፡፡

 

የሪዮ 5000ሜ የሴቶችን ዘርፍን ማን ያሸንፋል?

View Result