የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ሥራ አስፈጻሚ ቦርድ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ አባላት ጋር በስፖርት ልማት ዙሪያ መከረ

ደረጃ ያውጡለት
(0 ድምፆች)

የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ሥራ አስፈጻሚ ቦርድ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ አባላት ጋር በስፖርት ልማት ዙሪያ መከረ
በኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት ዶ/ር አሸብር ወልደጊዮርጊስ የተመራው የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ስራ አስፈጻሚ ቦርድ ሐምሌ 24 ቀን 2009 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ድሪባ ኩማ እና ከካቢኔ አባላት ጋር በከተማው የስፖርት መሠረተ ልማት ግንባታና የከተማውን ስፖርት ለማሳደግ በጋራ ስለሚሰሩባቸው ጉዳዮች መክረዋል፡፡
በውይይቱ መጀመሪያ ዶ/ር አሸብር ወልደጊዮርጊስ ለቦርዱ የተደረገውን ደማቅ አቀባበል አመስገነው
“የከተማ መስተዳድሩ የከተማውን ማህበረሰብ በተለይም ወጣቱን በስፖርት ተጠቃሚ ለማድረግ እያደረገ ያለው ጥረት እስከ ምን ድረስ ነው?::”
“የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለአዲስ አበባ ወጣቶች የስፖርት ልማት እንደ ወላጅ በመሆን አስፈላጊውን ትኩረት በመስጠት እየሰራ ነው ወይ?::”
“የከተማ መስተዳድሩ በተለይ ከሶስት አመት በኋላ ሀገራችን ለምትሳተፍበት የቶክዮ 2020 የኦሊምፒክ ጨዋታ የዕቅዱ አካል አድርጎ እየተንቀሳቀሰ ነው ወይ?::” ብለዋል፡፡


ዶ/ር አሸብር ወልደጊዮርጊስ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ከአቅም ግንባታ አኳያ አስፈላጊውን ድጋፍ ለከተማው ስፖርት እድገት እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡
የከተማው ከንቲባ አቶ ድሪባ ኩማ በበኩላቸው
“ስለሀገራችን ስፖርት ዕድገት በጋራ እንስራ ለማለት በከፍተኛ የስራ ተነሳሽነት ስለመጣችሁ በራሴ እና በከተማው ካቢኔ ስም ልባዊ ምስጋናዬ ይድረሳችሁ::”
“የስፖርት ልማትን ከወጣቱ ነጥሎ ማሰብ አይቻልም::”
“በከተማችን በተለያዩ አካባቢዎች በመገንባት ላይ የምንገኘው የስፖርት መሠረተ ልማቶች የከተማ አስተዳደሩ ለስፖርት ልማት ትኩረት መስጠቱን አመላካች ነው፡፡” ያሉት ከንቲባው ከኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ጋር እጅና ጎንት በመሆን ስፖርታችንን እና ለማለን በማለት አጽንኦት ሠጥተዋል፡፡
የከተማው ምክትል ከንቲባ አቶ አባተ ስጦታው በበኩላቸው
“አዲሱ የከተማችን ማስተር ፕላን በከተማችን ያለውን የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራ ችግር በከፍተኛ ደረጃ ይፈታል::”ብለዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በዋንኛነት ከ131 በላይ የ3 በ1 ሜዳዎች፣ ከ106 በላይ የወጣት ማዕከላት፣ የትልልቅ ስታዲየሞች፣ ከተማችን የኦሊምፒክ ስታንዳርድ ያሟላ የመዋኛ ገንዳ እና የጂምናዚየሞች ባለቤት ለመሆን ግንባታው እየተጠናቀቀ መሆኑን የከተማው የወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ንጋቱ ዳኛቸው ተናግረዋል፡፡
በውይይቱ በትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት አዘጋጅነት በመቀሌ ከተማ ለ6ኛው የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ጨዋታዎች የኢትዮጵያን ኦሊምፒክ ችቦ በቅብብሎሽ ከሚዞርባቸው የሀገራችን ከተሞች መካከል አንዷ አዲስ አበባ ከተማ መሆኗ ታውቋል፡፡
ከይዞታ ባለመብትነት ጋር ተያይዞ ሪቼ የሚገኘውን የመዝናኛ ማዕከል የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ በባለቤትነት ይዞ እንዲያስተዳድር በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ በተወሰነው መሰረት የከተማ መስተዳደሩ የባለቤትነት ካርታውን በተቻለ ፍጥነት ከሚኒስቴር መ/ቤቱ ወደ ብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴው እንዲያዘዋውር ተጠይቆ የባለቤትነት ማረጋገጫውን ሰነድ በቅርቡ ለኮሚቴው እንደሚስተላልፍ ተነግሯል፡፡
በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ የኦሊምፒክ አካዳሚ ለማስገንባት በይዞታነት በያዘው 120 ሺህ ካሬ ሜትር ላይ ካሳ ተሰጥቷቸው ያልተነሱ ሰዎች የሚነሱበት አግብብ እንዲፋጠን ተጠይቆ ከከተማ መስተዳድሩ ለጥያቄው አወንታዊ መልስ ተሰጥቷል፡፡
የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት ዶ/ር አሸብር ወልደጊዮርጊስ ከተማ አስተዳደሩ በስፖርት ልማት አበረታች ስራዎችን ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት እየሰራ እንደሚገኝና ይህው ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ የሥራ አስፈጻሚ በሀገራችን ክልሎች እና ከተሞች እያደረገ ያለውን የስራ ጉብኝቱን በአዲስ አበባ ከተማ በማድረግ ቋጭቷል፡፡

የሪዮ 5000ሜ የሴቶችን ዘርፍን ማን ያሸንፋል?

View Result