የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ሥራ አስፈጻሚ ቦርድ ከአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ካቤኔ ጋር በስፖርት ልማት ዙሪያ መከረ

ደረጃ ያውጡለት
(0 ድምፆች)

የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ሥራ አስፈጻሚ ቦርድ ከአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ካቤኔ ጋር በስፖርት ልማት ዙሪያ መከረ
በኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት ዶ/ር አሸብር ወልደጊዮርጊስ የተመራው የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ስራ አስፈጻሚ ቦርድ ሐምሌ 6 ቀን 2009 ዓ.ም በአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ርዕሠ መዲና በሆነችው ሠመራ በመገኘት የስራ ጉብኝት አደረገ፡፡
የስራ አስፈጻሚ ቦርዱ ከክልሉ ምክትል ርዕሠ መስተዳድር ከአቶ አወል አርባ እና ከክልሉ የካቤኔ አባላት ጋር በመገናኘት በክልሉ አጠቃላይ የስፖርት ልማት ስራ እንቅስቃሴ ላይ መክሯል፡፡  
በውይይቱ መጀመሪያ ዶ/ር አሸብር ወልደጊዮርጊስ ለቦርዱ የተደረገውን ደማቅ አቀባበል አመስገነው
“የክልሉ መንግስት የክልሉን ማህበረሰብ በተለይም ወጣቱን በስፖርት ተጠቃሚ ለማድረግ እያደረገ ያለው ጥረት እስከምን ድረስ ነው?::”
“የአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ለአፋር ወጣቶች የስፖርት ልማት እንደ ወላጅ በመሆን አስፈላጊውን ትኩረት በመስጠት እየሰራ ነው ወይ?::”
“አፋር ላይ እንደሌሎች ክልሎች የስፖርት አደረጃጀቶች ከታችኛው መወቃር (ቀበሌ) እንከ ላይኛው እርከን ድረስ በአግባቡ ተደራጅቷል ወይ?::”  የሚሉ ጥያቄዎችን ካነሱ በኋላ ፕሬዚዳንቱ በመቀጠል


“ከ800- 900 ሚሊየን ብር ወጪ ወጥቶ እየተገነባ ባለው ከትልቁ የሠመራ ስታዲየም ግንባታ በተጓዳኝ በአነስተኛ በጀት በስታዲየሙ ዙሪያ የአፋርን ወጣቶች የሚያሰባስብ ለስፖርቱ ልማት ወሳኝ የሆነ አንድ የስፖርት አካዳሚ ክልሉ ቢገነባ፡፡”
“ተቀናጅን ከሰሰራር ክልሉ በቶክዮ 2020 ኦሊምፒክ ሀገራቸውን የሚወክሉ አትሌቶች እንደሚያፈራ እምነቱ አለን፡፡”
“የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ከአቅም ግንባታ አኳያ አስፈላጊውን ድጋፍ ለክልሉ ያደርጋል፡፡ ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ተክለወይኒ አሠፋ በበኩላቸው
የክልሉ የስፖርት ባላደርሻ አካላት ከሠመራ ዩኒቭርስቲ ጋር ተቀናጅተው ለስፖርቱ ልማት መስራት እንደሚገባቸው አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡
የክልሉ ምክትል ርዕሠ መስተዳድር እና የስፖርት ምክር ቤት ሠብሳቢ አቶ  አወል አርባ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ በከፍተኛ ስራ ተነሻሽነት የስራ ጉበኝት ለማደረግ መምጣቱን ካመሰገኑ በኋላ
“በክልላችን በተለይ በእግር ኳስ፣ በአጭር ርቀት ሩጫ እና በዝላይ እምቅ አቅም ያላቸው ታዳጊ ወጣቶች እንዳሉ እናውቃለን::”
“ይሁን እንጂ ታዳጊ ወጣቶቻችን በስፖርት ተሳታፊ እና ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ምቹ መደላድል ፈጥረን በስፖርቱ የነቃ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ብዙ ርቀት አልተጓዝንም ስለሆነም ከስፖርት ልማት አኳያ ዕቅዶቻችንን መከለስ ይገባናል::”
 “የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ሥራ አስፈጻሚ ቦርድ አባላት የሰጡንን ገንቢ አስተያየቶች እንደቤት ስራ ወስደን የአቅዳችን አካል በማድረግ እንሰራለን::” ብለዋል፡፡
የክልሉ ካቤኔ ቀደም ሲል ለስፖርት የሚሰጠው ትኩረት አነስተኛ እንደነበር የተናገሩት ምክትል ርዕሠ መስተዳድሩ ካቢኔቸው ለስፖርት ልማት የሚሰጠውን ትኩረት እንደሚያጠናክር ቃል ገልተዋል፡፡
የክልሉ የወጣቶችና ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ማዕረ አሊሲሮ በበኩላቸው
“በክልላችን የስፖርት ልማቱን የሚሳልጡ ፕሮጅክቶችን እናሰፋፋለን፡፡”
“በክልላችን ያሉትን የስፖርት እምቅ አቅሞች በጥናት እንለያለን፡፡”
“የሀገር ውስጥ እና የአለም አቀፍ ውድድሮችን በሠመራ ለማዘጋጀት ራዕይ ሰንቀናል፡፡”
“ከኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ጋር ተቀራርበት በመቀናጀት እንሰራለን::” ብለዋል፡፡
በውይይቱ ለ6ኛው የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ጨዋታዎች የኢትዮጵያን ኦሊምፒክ ችቦ በቅብብሎሽ ከሚዞርባቸው የክልል ከተሞች መካከል አንዷ ሠመራ መሆኗ ታውቋል፡፡
ከውይይቱ በመቀጠል የሥራ አስፈጻሚ ቦርዱ ከ800 እስከ 900 ሚሊዮን ወጪ በመገንባት ላይ የሚገኘውን የሰመራን ኢንተርናሽናል ሰታዲየም ጎብኝቷል፡፡
ቦርዱ በመጨረሻም የክልሉን የወጣቶችና ስፖርት ኮሚሽን እና አንድ ጂምናዝየም በመጎብኘት የሥራ ጉብኝቱን አጠናቋል፡፡
የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ የሥራ አስፈጻሚ በሀገራችን ክልሎች እና ከተሞች እያደረገ ያለውን የስራ ጉብኝቱን ከአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር ጋር በማድረግ እንደሚቋጭ ታውቋል፡፡

የሪዮ 5000ሜ የሴቶችን ዘርፍን ማን ያሸንፋል?

View Result