የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ሥራ አስፈጻሚ ቦርድ የአምቦ የእግር ኳስ ማሠልጠኛ ማዕከል ጎል ፊፋን እና የሱሉልታ ኦሮሚያ ስፖርት አካዳሚን ጎበኘ

ደረጃ ያውጡለት
(0 ድምፆች)

የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ሥራ አስፈጻሚ ቦርድ የአምቦ የእግር ኳስ ማሠልጠኛ ማዕከል ጎል ፊፋን እና የሱሉልታ ኦሮሚያ ስፖርት አካዳሚን ጎበኘ

በኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት ዶ/ር አሸብር ወልደጊዮርጊስ የሚመራው ስራ አስፈጻሚ ቦርድ ሠባተኛ የሆነውን የስራ ጉብኝቱን በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት እያደረገ ይገኛል፡፡

ቦርዱ በመጀመሪያ ቀን (ሠኔ 12 ቀን 2009 ዓ.ም) የስራ ጉብኝቱ አምቦ የሚገኘውን በ2005 ዓ.ም ስራ የጀመረውን የአምቦ የእግር ኳስ ማሠልጠኛ ማዕከል ጎል ፊፋን ጓብኝቷል፡፡

ማዕከሉ በ2008 ዓ.ም. በመጀመሪያ ዙር ከ17 ዓመት በታች 27 ወንዶች እና 22 ሴቶችን በድምሩ 49 ሠልጣኞችን አስመርቋል፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ የተመረቁት ሠልጣኞች በተለያዩ ክለቦች እንደገቡ ታውቋል፡፡

ማዕከሉ በአሁኑ ወቅት የወቅቱን ዘመናዊ የስፖርት ሳይንስ ማዕከል አድርጎ በተቀረጸ ካሪኩለም ከ15 እና ከ17 ዓመት በታች 30 ወንዶች እና 24 ሴቶች በድምሩ 54 ልጆችን ተቀብሎ እያሰለጠ መሆኑን የማዕከሉ ዳይሬክተር አቶ ሙሊሳ ለሜሳ ተናግረዋል፡፡ 

የሥራ አስፈጻሚ ቦርዱ በማዕከሉ በመሰልጠን ላይ ያሉ ልጆችን ባነጋገረበት ወቅት የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት ዶ/ር አሸብር ወልደጊዮርጊስ

“እንደዚህ አይነት ማዕከል እና እናተን ተስፋ ያላችሁን ታዳጊ ወጣቶች ማየቴ በጣም አስደስቷኛል፡፡”

“ጠንክራችሁ ከሠራችሁ በቶክዮ 2020 ኦሊምፒክ ጨዋታዎች ለሀገራችን ብሔራዊ ቡድን የመጫወት እድሉ አላችሁ፡፡”

“የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ይህ እውን እንዲሆን አቅም በፈቀደ አግባብ ሁለገብ ድጋፉን ያደርግላችኋል…ከጎናችሁ ነን፡፡” ብለዋል፡፡

 

የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ተስፋዬ ይገዙ በበኩላቸው

“ስፖርትን ዝንባሌን ማዕከል አድርጎ ማሠልጠን በሀገራችን ብዙም የተለመደ አይደለም፡፡”

“የውስጣችሁ ፍላጎት አና ዝንባሌ ታይቶ ወደዚህ ታላቅ ማዕከል መጥታችኋል፡፡ እድለኞች ናችሁ፡፡ ጠንክራችሁ ሰርታችሁ በእግር ኳሱ ሀገራችንን እንደምታኳሩ እምነቴ የጸና ነው፡፡”

“ለስነምግባር እና ለስፖርታዊ ጨዋነት የተገዛችሁ ሁኑ፡፡” ብለዋል::

በማዕከሉ በመሰልጠን ላይ የሚገኙት ታዳጊ ወጣቶች በንድፈ ሃሳብ እና በተግባር ተደግፈው በሳምንት የ6 ቀናት ስልጠና እየወሰዱ መሆኑ ታውቋል፡፡   

ቦርዱ በሁለተኛ ቀን (ሠኔ 13 ቀን 2009 ዓ.ም) የስራ ጉብኝቱ ደግሞ ግንባታው 41.6 በመቶ የተጠናቀቀውን የሱሉልታ ኦሮሚያ ስፖርት አካዳሚን ጎብኝቷል፡፡

በ2008 ዓ.ም ግንባታው የተጀመረው አካዳሚ በአንድ ጊዜ 600 ሠልጠኞችን ተቀብሎ በ13 የስፖርት አይነቶች ማሰልጠን አቅም አለው፡፡

የኦሮሚያ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ በኃላፊነት ተቀብሎ የሚያስተዳድረው የሱሉልታ ኦሮሚያ ስፖርት አካዳሚ ጠቅላላ የተመደበለት በጀት 713 ሚሊዮን ብር እንደሆነ ታውቋል፡፡

የሁለቱም ጾታዎች የማደሪያ ክፍሎች፣ የመማሪያ ክፍል፣ የአሠልጣኞች እና የዳይሬክተሮች መኖሪያ እና ሌሎች መሰል አገልግሎት መስጫ ያለው አካዳሚ በ2010 ዓ.ም. ሰኔ ወር ላይ ግንባታው ተጠናቆ ወደ ስራ እንደሚገባ ተነግሯል፡፡

የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ከሚቴ ሥራ አስፈጻሚ ቦርድ የአዳማ ሣይንስ እና ቴክኖሎጂ የስፖርት መሠረተ ልማት እና የከተማውን ስታዲምየም ይጎበኛል፡፡

ወደፊት በሚወሰን ቀን ደግሞ የሥራ አስፈጻሚ ቦርዱ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ርዕሠ መስተዳደር እና የካቤኔ አባላትን በሀገራችን የስፖርት እድገት ዙሪያ የክልሉን ዝግጅት እና አስተዋጽኦ አስመልክቶ ውይይት እንደሚደረግ ይጠበቃል፡፡  

የዜና ምንጭ፣ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ የኮሙኒኬሽን ክፍል 

 

የሪዮ 5000ሜ የሴቶችን ዘርፍን ማን ያሸንፋል?

View Result