የአትሌት መሠረት ደፋር የቤጂንግ አሊምፒክ ሜዳሊያ ወደ ብር አደገ

ደረጃ ያውጡለት
(0 ድምፆች)

ፕሬስ ሪሊዝ

እንደደረሠ ጥቅም ላይ የሚውል

የአትሌት መሠረት ደፋር የቤጂንግ አሊምፒክ ሜዳሊያ ወደ ብር አደገ

የአለም አቀፍ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ለኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ በጻፈው ደብዳቤ ሀገራችን ከተሳተፈችባቸው የአትሌቲክስ “ኢቨንቶች” መካከል በሴቶች የ5 ሺ ሜትር የሩጫ ውድድር አትሌት መሠረት ደፋር በወቅቱ ያገኘችው የነሐስ ሜዳሊያ ወደ ብር ሜዳሊያ ማደጉን አስታወቀ፡፡

በቤጂንጉ 29ኛው ኦሊምፒያድ የአትሌት መሠረት ደፋር ውጤት የተሻሻለው በወቅቱ ቱርኳዊቷ ሯጭ ኤልቫን አብይ ለገሰ የተከለከለ ንጥረ ነገር (ያልተፈቀደ አበረታች ንጥረ ነገር) ተጠቅማ በመገኘቷ ነው፡፡

በተሻሻለው ውጤት መሠረት በሴቶች 5 ሺህ ሜትር ሩጫ የአትሌት ጥሩነሽ ዲባባ ወርቅ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ የመሠረት ደፋር ብር እና በወቅቱ አራተኛ ደረጃ ይዛ የነበረችው ኬንዊቷ ሲሊቪያ ኬቤት ሶስተኛ ደረጃን ተጓናጽፋ የነሀሰ ሜዳሌያውን ታገኛለች፡፡

አትሌት መሠረት ደፋር በቤጂንግ ኦሊምፒክ የገባችበት ሠዓት 15 ደቂቃ ከ 44.12 ሴኮንዶች ነበር፡፡የአለም አቀፍ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ለኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ በጻፈው ደብዳቤ አትሌት መሠረት ደፋር በወቅቱ የተሸለመችውን የነሐስ ሜዳሊያ፣ ዲፕሎማ እና የነሐስ ሜዳሊስት ፒን በብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴው በኩል እንድትመልስ ተደርጎ በቅርቡ የብር ሜዳሊያዋ እንደሚተካ ታውቋል፡፡

በዚህ አግባብ ሀገራችን በወቅቱ በዓለም 18 (አስራ ስምንተኛ) ደረጃ የያዘችው ደረጃ ይሻሻላል ተብሏ ይጠበቃል፡፡

በተሻሻለው ውጤት መሠረት በቤጂንግ ኦሊምፒክ ሀገራችን በተወዳደረችባቸው ውድድሮች በአትሌት ጥሩነሽ ዲባባ በ10 ሺ እና በ5 ሺ ውድድሮች ሁለት ወርቅ፣ በአትሌት ቀነኒሳ በቀለ በ10 ሺ እና በ5ሺ ሁለት ወርቅ መገኘቱ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ በአትሌት መሠረት ደፋር የብር ሜዳሊያ፣ በአትሌት ስለሺ ስህን በ10 ሺ ሜትር የብር ሜዳሊያ፣ እንዲሁም በአትሌት ፀጋዬ ከበደ በማራቶን የነሐስ ማዳሊያ በድምሩ ሀገራችን ሰባት ሜዳሊያዎችን አግኝታለች፡፡

ከዚህ ቀደም አትሌት ሶፍያ አሠፋ በለንደን 2012 ኦሊምፒክ ጨዋታዎች በሴቶች የ3000 ሜትር የመሠናክል ውድድር በወቅቱ ያገኘችው የነሐስ ሜዳሊያ ወደ ብር ሜዳሊያ እንዲያድግ መደረጉ ይታወሳል፡፡

አትሌት መሠረት ደፋር የተሻሻለው የብር ሜዳሊያ ከአለም ኦሊምፒክ ኮሚቴ እንደመጣ በደማቅ ስነ-ስርዓት ሜዳሊያዎን እንደምትረከብ ኮሚቴው አስታውቋል፡፡

የተስተካከለው ውጤት ታርሞ ሀገራችን እስካሁን በተሳተፈችባቸው 13 የኦሊምፒክ ጨዋታዎች (ኦሊምፒያድ) 22 የወርቅ፣ 11 የብር፣ እና 20 የነሐስ በድምሩ 53 (ሀምሳ ሶስት ሜዳሊያዎችን) ሠብስባለች፡፡

ቱርኳዊቷ ሯጭ ኤልቫን አብይ ለገሰ የተከለከለ ንጥረ ነገር በመጠቀሟ ሳቢያ እ.ኤ.አ ከ 2007 እስከ 2009 ድረስ ያለው ክብሯ፣ ጥቅሟና ሁሉም ሜዳሊያዎችዋ ተገፈዋል፡፡
=30=

የሪዮ 5000ሜ የሴቶችን ዘርፍን ማን ያሸንፋል?

View Result