የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ሥራ አስፈጻሚ ቦርድ ሁለተኛውን የሥራ ጉብኘት ከአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ጋር አካሄደ

ደረጃ ያውጡለት
(0 ድምፆች)የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ሥራ አስፈጻሚ ቦርድ ሁለተኛውን የሥራ ጉብኘት ከአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ጋር አካሄደ

የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ሥራ አስፈጻሚ ቦርድ በሁለተኛው የስራ ጉብኝቱ በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ግንቦት 10 ቀን 2009 ዓ.ም በመገኘት ከክልሉ መንግስት ጋር በስፖርት ልማት ዙሪያ መከረ፡፡

የኮሚቴው ሥራ አስፈጻሚ ቦርድ ግንቦት 9 ቀን 2009 ዓ.ም የክልሉ መዲና በሆነቸው ባህር ዳር ሲገባ በክልሉ አመራሮች ደማቅ አቀባበል ተደርጎለታል፡፡

የሥራ አስፈጻሚ ቦርዱ የባህር ዳር አለም አቀፍ ሁለገብ ስታዲየም እና በባህር ዳር ዩኒቭርስቲ የስፖርት አካዳሚን የስፖርት መሰረተ ልማቶች ጎብኝቷል፡፡

  የኮሚቴው የስራ አስፈፃሚ ቦርድ አባላት የባህር ዳር ሁለገብ ስቴድየም እና የባህርዳር  ዩኒቨርስቲ ስፖርት አካዳሚ ከጎበኙ በኋላ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዘዳንት ዶክተር አሸብር ወልደጊዮርጊስ ጉብኝቱ ክልሉ በስፖርቱ ዘርፍ ያለበትን ደረጃ ለማወቅ እንዳስቻላቸው ገልፀዋል።«የቶክዮ 2020 ኢሊምፒክ፤ 12ኛው መላ አፍሪካ ጨዋታ፤ የአለም የወጣቶች ኦሊምፒክ፣ የአፍሪካ ወጣቶች ኦሊምፒክ ጨዋታዎች እና ሌሎች ታላላቅ ዓለማቀፍ ውድድሮች ከፊታችን አሉ» ያሉት ዶክተር አሸብር እንዲህ አይነት ጉብኝት ማድረጉ ከክልሎች ጋር ከወዲሁ ተቀራርቦ ለመስራት እንደሚጠቅም አስረድተዋል።

   የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ለኢትዮጵያ ስፖርት ታላላቅ ስፖርተኞችን ከማበርከት ባለፈ ኦሊምፒክን የመሳሰሉ ዓለማቀፍ ውድድሮች ሲደርሱ ከፋይናንስ ጀምሮ ድጋፍ በማድረግ በአገራችን ስፖርት ትልቅ ድርሻ እንዳለው አብራርተዋል።

    በጉብኝቱ በርካታ ግብዓቶችን እንዳገኙ የገለፁት ዶክተር አሸብር ወልደጊዮርጊስ የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የስፖርት ምሁራንን መጠቀም የሚያስችል መንገድ እንደተፈጠረም አብራርተዋል። መንግስት በክልሉ ወጣቶችና የማዘውተሪያ ስፍራዎች ላይ ትኩረት አድርጎ ያከናወናቸው ስራዎች አበረታች ውጤት እያመጡ መሆኑንም ገልፀዋል። የክልሉ የስፖርት ቢሮና የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ከኦሊምፒክ ኮሚቴ ጋር በጥምረት የሚሰራበት መልካም አጋጣሚ እንደተፈጠረም ተናግረዋል።የኮሚቴው ሥራ አስፈጻሚ ቦርድ በዕለቱ የመጨረሻ ውሎው ከአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው እና የካቢኔ አባላት ጋር ውይይት አድርገዋል፡፡ ክልሉ ባዘጋጀው የራት ግብዣ ላይ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ፣ ክልሉና ሌሎች ባለድርሻ አካላት የኢትዮጵያን ስፖርት እድገት ከማጠናከር አኳያ ምን አይነት ስልት በጋራ በመንደፍ መንቀሳቀስ እንዳለባቸው መክረዋል፡፡

የክልሉ ርዕሠ መስተዳርድ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው “ኦሊምፒክ ኮሚቴ በኦሊምፒክ መርህ መሰረት በተለያዩ ክልሎች የሚያዘጋጀው የመላ ኢትዮጵያ ጨዋታዎች ብሔር ብሔረሰቦች፤ በተለይም ወጣቶች ባህልና ልምዳቸውን እንዲለዋወጡ አስችሏል::”

“የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ከክልሉ ጋር አብሮ ለመስራት ያሳየውን ተነሳሽነት ሊያጠናክር ይገባል ብለዋል። ብለዋል፡፡

በምክክሩ ሀገራችን ስለ 6ኛው የመላ ኢትዮጵያ ጨዋታዎች እና ሀገሪቷ በአራት ዓመት ስትራቴጂክ ዘመን ውስጥ በአለም አቀፍ ደረጃ ስለምትወዳደርባቸው ውድድሮች ዝግጅት እና ተሳትፎ ውይይቶች ተካሂደዋል፡፡ አገራችን በስትራቴጂክ ዘመኑ በምታደርጋቸው ወድድሮች ማለትም እ.ኤ.አ 2018 አልጀረስ ላይ ስለሚካሄደው 3ኛው የአፍሪካ ወጣቶች ጨዋታዎች፣ 12ኛው የመላ አፍሪካ ጨዋታዎች፣ 2019 ኬፕ ቬርዴ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ስለሚካሄደው የቢች (Beach) ጨዋታዎች፣ 2018 ቦነስ አይረስ ላይ ስለሚዘጋጀው የአለም ወጣቶች ኦሊምፒክ እና 2020 ላይ ቶክዮ ላይ ስለሚደርገው 32ኛው ኦሊምፒያድ ዝግጅትንና ሌሎች ጉዳዮች ላይ ምክከር አድርገዋል፡፡
 
የክልሉ መንግስት የኢትዮጵያን ኦሊምፒክ ኮሚቴ የሥራ ጉብኝት በማድነቅ፣ ከኮሚቴው ጋር በመቀናጀት ለሀገራችን የስፖርት ልማት ዕድገት የበኩሉን ሚና እንደሚጫወት ቃል ገብቷል፡፡  

በምክክሩ ላይ የ.ኢ.ፌ.ዲ.ሪ ወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ተስፋዬ ይገዙ እና የክልሉ ካቢኔ አባላት ታዳሚዎች ነበሩ፡፡
 

የሪዮ 5000ሜ የሴቶችን ዘርፍን ማን ያሸንፋል?

View Result