ከአራት ዓመታት በኋላ አትሌት ሶፍያ አሠፋ የለንደን 2012 ኦሊምፒክ የብር ሜዳሊያ በደማቅ ሥነ-ሥርዓት ልታጠልቅ ነው

ደረጃ ያውጡለት
(0 ድምፆች)

ከአራት ዓመታት በኋላ አትሌት ሶፍያ አሠፋ የለንደን 2012 ኦሊምፒክ የብር ሜዳሊያ በደማቅ ሥነ-ሥርዓት ልታጠልቅ ነው

ሀገራችን ለ12ኛ ጊዜ በተሳተፈችበት የለንደን 2012 ኦሊምፒክ ጨዋታዎች ከተሳተፍንባቸው የአትሌቲክስ “ኢቨንቶች” መካከል በሴቶች የ3000 ሜትር የመሠናክል ውድድር አትሌት ሶፊያ አሠፋ በወቅቱ ያገኘችው የነሐስ ሜዳሊያ ወደ ብር ሜዳሊያ ከፍ አለ፡፡

በሀገራችን የኦሊምፒክ ታሪክ ከ32 ዓመታት በኋላ (የሞስኮ 1972 ኦሊምፒክ) በመሠናክል ውድድር የአትሌት እሸቱ ቱራን ገድል የደገመችው አትሌት ሶፍያ በለንደኑ ኦሊምፒክ የሜዳሊያ ሽልማት ወቅት ያጠለቀችው የነሐስ ሜዳሊያ ድካሟን እና ትጋቷን እንደማይመጥን ተገለጸ፡፡

 የአለም ኦሊምፒክ ኮሚቴ በቤጂንግ እና በለንደን ኦሊምፒክ ጨዋታዎች ተሳታፊ ከነበሩ ከ1000 በላይ አትሌቶች ላይ ባደረገው ዳግም የደም ናሙና ምርመራ አትሌታችን ሶፊያ አሰፋ በተወዳደረችበት የ3000 የመሠናክል ውድድር ላይ በወቅቱ አንደኛ ወጥታ የወርቅ ሜዳሊያ ያጠለቀችው ሩሲያዊቷ አትሌት ዮሊያ ዛራፖቫ (Yuliya Zaripova) ስትሪዮድ ትሪናቦል (Steroid Turinabol) የተባለ የተከለከለ ንጥረ ነገር ተጠቅማ ስለተገኘች የአትሌቷ ውጤት በመሰረዙ ምክንያት የውጤት ሽግሽግ (ማሻሻያ) መደረጉ ተነግሯል፡፡

በውጤቱ ለውጥ ሳቢያ ቱኒዛዊቷ አትሌት ሀቢባ ጋራቢ የወርቅ፣ ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ሶፍያ አሠፋ የብር፣ እና ኬንያዊቷ አትሌት ሚልካ ቼሞዝ የነሐስ ሜዳሊያዎችን እንዲያገኙ ተወስኗል፡፡

የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ በተስተካከለው አዲስ አመርቂ የውጤት ማሻሻያ እንኳን ደስ አለን እያለ፣ ሐሙስ ጥር 25 ቀን 2009 ዓ.ም ከጠዋቱ 4፡30 ሠዓት ላይ ለብርቅዬዋ አትሌት የሜዳሊያ ሽልማት ሥነ-ስርዓት ያከናውናል፡፡
በኢትዮጵያ የኦሊምፒክ ታሪክ በ3000 ሜትር የመሰናክል ውድድር የመጀመሪያ የሆነችው አትሌት ሶፍያ አሠፋ በለንደን ኦሊምፒክ የገባችበት ሠዓት 9 ደቂቃ ከ 06.72 ሴኮንዶች ነበር፡፡

አትሌቷ በመላ አፍሪካ ጨዋታዎች፣ በአፍሪካ እና በአለም ሻምፒዮናዎች ላይ በመሳተፍ ለሀገሯ አኩሪ ድሏችን አስመዝግባለች፡፡ ለአብነት ያህል ባለፈው አመት በኮንጎ ብራዛቪል ላይ በተካሄደው የ3000 መሰናክል ውድድር የወርቅ ሜዳሊያ እና በ2013 በሞስኮ በተካሄደው የአለም ሻምፒዮ ላይ የነሐስ ሚዳሊያ ማስመዝገቧ ይታወሳል፡፡


የተከለከለ አበረታች ንጥረ ነገር በሽንት ምርመራ የተገኘባት ሩሲያዊቷ አትሌት ዮሊያ ዛራፖቫ  ከአትሌቲክስ ስፖርት ከማታገዷ በተጨማሪ እ.ኤ.አ ከ ጁላይ 2011 እስከ ጁላይ 2013 ያገኘቻቸው ክብሮች፣ ሜዳሊያዎች እና ጥቅሞች ሙሉ ለሙሉ ተሰርዘውባታል፡፡
 
ኢትዮጵያ በለንደኑ ኦሊምፒክ ጨዋታዎች በአትሌቲክስ ስፖርት ከ400 ሜትር እስከ ማራቶን ድረስና በውሃ ዋና ስፖርቶች በመሳተፍ በድምሩ ባገኘችው 7 ሜዳሊያዎች ከዓለም 24ኛ ከአፍሪካ 2ኛ በመውጣት በኦሊምፒክ መድረክ ክብሯን ማስጠበቋ ይታወሳል፡፡

የተስተካከለው ውጤት ታርሞ ሀገራችን እስካሁን በተሳተፈችባቸው 13 የኦሊምፒክ ጨዋታዎች (ኦሊምፒያድ) 22 የወርቅ፣ 10 የብር፣ እና 21 የነሐስ በድምሩ 53 (ሀምሳ ሶስት ሜዳሊያዎችን) ሠብስባለች፡፡

የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ እ.ኤ.አ ከ2017 እስከ 2020 የስትራቴጂክ ዕቅድ ዘመኑ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት በሀገራችን ስፖርት ላይ ጥቁር ጥላውን ያጠላውን ከኃይል ሠጪና አበረታች መድሃኒቶች ጋር ተያይዞ የተፈጠረውን የቀውስ አዝማሚያ ለመታገል ዝግጅቱን ማጠናቀቁን አስታውቋል፡፡  

Total votes : 9
Return to Poll