ማርሽ ቀያሪው የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ቤተሰብ ከዚህ አለም በሞት ተለየ

ደረጃ ያውጡለት
(0 ድምፆች)

ማርሽ ቀያሪው የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ቤተሰብ ከዚህ አለም በሞት ተለየ

የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን ገለጸ

 

በሩጫ ህይወቱ “ማርሽ ቀያሪው” ተብሎ እስከ መጠራት የደረሰው አንጋፋው አትሌት እና አሠልጣኝ ምሩጽ ይፍጠር በተወለደ በ72 ዓመቱ በካናዳ-ቶሮንቶ ትላንት ማለዳ ታህሳስ 14 ቀን 2009 ዓ.ም ህይወቱ አለፈ፡፡

 


ለአትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ እና ለሌሎች ብርቅዬ አትሌቶች አርአያ የነበረው ታላቁ አትሌት በኦሊምፒክ መድረክ ብቅ ያለው በሙኒክ የበጋ ኦሊምፒክ ሲሆን፣ በ10 ሺ ሜትር ነሐስ ሜዳሊያ ለሀገሩ ሲያስገኝ፣ ከአራት አመት በኋላ በ1980 ሞስኮ በተካሄደው የኦሊምፒክ ጨዋታ በ10 ሺ እና በ5 ሺ ሜትር በሁለቱም ኩነቶች የወርቅ ሜዳሊያዎች ሲያመጣ በተለይም በ5ሺ ሩጫ ውድድር ወቅት በመጨረሻ ዙር ባሳየው የአጨራረስ ብቃት በወቅቱ የነበሩ የዓለም መገናኛ ብዙሃን“ ማርሻ ቀያሪው ይፍጠር” ብለው አወድሰውት ነበር፡፡
ሻምበል አትሌት ምሩጽ ይፍጠር እ.ኤ.አ በ1973 ሌጎስ ላይ በተካሄደው የመላ አፍሪካ ጨዋታዎች በ10 ሺ የወርቅ፣ በ5 ሺህ የብር ሜዳሊያዎችን ለሀገሩ ሲያስገኝ፣ በአለም አቀፉ የአትሌቲክስ ማህበር እ.ኤ.አ በ1977 እና በ1979 ባዘጋጀው የአለም ሻምፒዮና ላይ በ10 ሺ እና 5 ሺ ሩጫ ውድድር የወርቅ ሜዳሊያዎችን አስገኝቷል፣ እንዲሁም በ1980ዎቹ በተሳተፈባቸው በርካታ የዓለም አቀፍ ሻምፒዮናዎች ላይ ተወዳድሮ አሸናፊ በመሆን ሀገሩን አስጠርቷል፡፡
የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ በዚህ ጀግና ህልፈት የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን ገልጾል፡፡ የኮሚቴው ኤግዚኪዮቲቭ ዳይሬክተር አቶ ታምራት በቀለ“ የአትሌቱን ዜና ዕረፍት የሰማነው በታላቅ ሀዘን ውስጥ ሆነን ነው፡፡”
“ይህንን የኦሊምፒክ ቤተሰብ የምንግዚም ጀግና በማጣታችን ጥልቅ ሀዘን ተሰምቷናል፡፡”
“ምሩጽ ለሀገሩ እና ለህዝቡ በሰራው ውለታ ታሪክ ሲዘክረው ይኖራል፡፡ ለመላው ቤተሰቦቹ፣ አድናቂዎቹ፣   ወዳጆቹ እና በአጠቃላይ ለኦሊምፒክ ቤተሰብ በኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ስም መጽናናትን እንመኛለን::”ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ የዚህን ብርቅዬ አትሌት ህይወት ለመታደግ ለህክምና ወጪ የሚሆን የገንዘብ ድጋፍ ማድረጉ ይታወሳል፡፡

Total votes : 9
Return to Poll