የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ 2ኛውን የሀገር አቀፍ ጨዋታ አስመልክቶ የፓናል ውይይት አካሄደ

ደረጃ ያውጡለት
(0 ድምፆች)

የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ከታህሳስ 8 እስከ 16 ቀን 2009 ዓ.ም ድረስ የተዘጋጀውን ሁለተኛውን ሀገር አቀፍ የሴቶች ጨዋታዎችን አስመልክቶ ሴቶች በስፖርት እና በኦሊምፒክ እንቅስቃሴ ውስጥ ያላቸውን ሚና እንዲያጎለብቱ የግማሽ ቀን የፓናል ውይይት አካሄደ፡፤


በመድረኩ ኦሊምፒዝም እና የሴቶች ሚና በኦሊምፒክ እንቅስቃሴ፣ ሴቶች እና የመገናኛ ብዙሃን፣ እንዲሁም ሴቶችን በስፖርት እንቅስቃሴ ማብቃት የሚሉ ርዕስ ጉዳዮች ላይ ጥናታዊ ጹሁፎች ቀርበው ሰፋ ያለ ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፤
በፓናል ውይይቱ ጥናታዊ ጹሁፎቹን ያቀረቡት በኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ የሴቶች እና ስፖርት ኮሚሽን አባል እና የኮሙኒኬሽን ባለሙያ በሆኑት ወ/ሮ መሠረት ደምሱ ፣ በኮሚቴው የኮሚሽኑ ፀሀፊ እና የሰው ሃብት አስተዳደር በሆኑት ወ/ት ፅጌ ለሚ እና  በኮሚሽኑ አባል እና በወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር የሴቶች ማብቃት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር በሆኑት በወ/ሮ ስንታየሁ ፍ/ዩሐንስ ነበር፡፡
በመድረኩ ላይ ከዘጠኙም የሀገሪቷ ክልሎችና ሁለት የከተማ አስተዳደሮች የመጡ ሴት አትሌቶች፣ የቡድን መሪዎች፣ አሠልጣኞች፣ እና የሐረሪ ህዝብ ክልላዊ መንግስት ከፍተኛ አመራሮች በአጠቃላይ ከሁለት ሺህ በላይ ተሳታፊዎች ተገኝተዋል፡፡
የፓናል ውይይቱን የመሩት የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ኤግዚኩዩቲቭ ዳይሬክተር አቶ ታምራት በቀለ “ያለሴቶች የነቃ ተሳትፎ እና አመራር የስፖርት ዘርፋችን ያድጋል ብንል የቀን ቅዠት ነው”
“የዚህ ፓናል ውይይት መድረክ አላማ በአለም፣ በአህጉር እና በተለይ በሀገራችን ያለውን የሴቶች የስፖርት እንቅስቃሴ በወፍ በረራ ቅኝት በማሳየት በርካታ ሴት ስፖርተኞችን እና አመራሮችን ለመፍጠር ያለመ ነው” ብለዋል፡፡  
በፓናሉ ላይ  የታደሙት የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ዘርፍ ሚኒስትር ደኤታ አቶ ተስፋዬ ይገዙ፣ የክልሉ የስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ያየህ ዘካርያ እና የሴቶችና ህፃናት ቢሮ ኃላፊ እና የ2ኛው ሀገር አቀፍ የሴቶች ጨዋታ ዝግጅት አጠቃላይ አብይ ኮሚቴ ሠብሳቢ ወ/ሮ ሀናን ዱሪ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ይህን የመሰለ ታላቅ መድረክ በማዘጋጀቱ ምስጋናቸውን ችረውታል፡፡
በመጨረሻም በፓናሉ ማጠቃለያ የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ዘርፍ ሚኒስትር ደኤታ አቶ ተስፋዬ ይገዙ ለዘጠኝ ተከታታይ ቀናት የሚካሄደው የሴቶች ስፖርት ጨዋታ ፍጹም ሠላማዊ፣ ማራኪ እና የህዝቦችን አንድነት አጠናክሮ እንዲጠናቀቅ ጨዋታው ስፖርታዊ ጨዋነትን ማዕከል አድርጎ መካሄድ እንዳለበት አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡
ጨዋታው በወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር እና በኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ በጋራ የተዘጋጀ ነው፡፡

የሪዮ 5000ሜ የሴቶችን ዘርፍን ማን ያሸንፋል?

View Result