የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ የሪዮ ኦሊምፒክ ልዑክ ቡድንን ይፋ አደረገ

ደረጃ ያውጡለት
(0 ድምፆች)

የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ሐምሌ 12 ቀን 2008 ዓ.ም በራማዳ አዲሰ አበባ ሆቴል በሠጠው ጋዜጣዊ መግለጫ የሪዮ 2016 የሚጓዙ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ልዑካንን ይፋ አድርጓል፡፡

ከሐምሌ 29 ቀን 2008 ዓ.ም ጀምሮ በብራዚል አስተናጋጅነት በሪዮ ዴ. ጄኔሮ ከተማ በሚካሄደው 31ኛው ኦሊምፒያድ ላይ ኢትዮጵያ በውሃ ዋና፣ ብስክሌት እና በአትሌቲክስ የኦሊምፒክ ስፖርቶች በ38 አትሌቶች እንደምትወከል ታውቋል፡፡

ከአትሌቶቹ ጋር አሠልጣኞች፣ ወጌሾች እና የቡድኑን ሐኪሙን ጨምሮ 22 የልዑካን ቡድን በድምሩ ከ60 በላይ የሚሆኑ የልዑካን ቡድን ወደ ብራዚሏ መዲና ሪዮ ዴ.ጄኔሮ ያመራሉ፡፡

የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሜቴ ኤግዚኩዩቲቭ ዳይሬክተር እና የሪዮ 2016 የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ  ቡድን መሪ አቶ ታምራት በቀለ፣

“የልዑካን ቡድኑ ቁጥር በአለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ አማካኝነት የሚጋበዙ ከፍተኛ የመንግስት አመራሮችን፣ ጋዜጠኞችን እንዲሁም በራሳቸው ተነሳሽነት ወጪያቸውን ሸፍነው ቡድኑን ለመደገፍ የሚሄዱትን አያካትትም” ብለዋል፡፡ 

በመግለጫው የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ከዲዛይነር ማፊ ጋር በጋራ በመተባበር የሀገሪቱን ብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦችን ባህል ማዕከል አድርጎ ያሠራውን የባህል ልብስ አስመርቋል፡፡

የባህል ልብሱ የሪዮ 2016 የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ልዑክ ቡድን የሪዮ 2016 ኦሊምፒክ ጨዋታዎች በሚጀመርበት እና በሚጠናቀቅበት ቀን የሚለበስ እንደሆነ ተነግሯል፡፡ 

ከዚህ ጋር ተያይዞ በአዲስ ዲዛይን እና አቀራረብ በአዲዳስ ኩባንያ ተዘጋጅቶ የቀረበው የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ስፖርት አልባሳት ይፋ ተደርገዋል፡፡ ይፋ የተደረጉት የስፖርት አልባሳት አትሌቶች በመኖሪያ ካምፕ፣ በውድድር እና በጋዜጣዊ መግለጫ ወቅት የሚለብሱት አልባሳት ናቸው፡፡

በመግለጫው ላይ ለአመርቂ ውጤት የሚጠበቁት አትሌት አልማዝ አያና፣ ገለቴ ቡርቃ፣ መሐመድ አማን፣ እና ደጀን ገብረመስቀል የታደሙ ሲሆን ዝግጅታቸውን እያገባደዱ እና ጥሩ ውጤትም ለማምጣት እንደሚተጉ ተናግረዋል፡፡    

 

የሪዮ 5000ሜ የሴቶችን ዘርፍን ማን ያሸንፋል?

View Result