Archived Articles

የኢትዮጵያ ቦውሊንግ አሶሴሽን

የኢትዮጵያ ቦውሊንግ አሶሴሽን የተቋቋመው ከ50 ዓመት በላይ ሲሆን የአለም ቦውሊንግ አሶሴሽን አባል በመሆን ከአንድ ውድድር ዓመት በቀር በየአመቱ የሚካሄድ የአለም አቀፍ የቦወሊንግ ውድድር ላይ በመሳተፍ ሀገራችን ከስፖርቱ ልታገኝ የምትችለውን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንድታገኝ በጣም ከፍተኛ አስተዋጽ ሲያበረክት የቆየ አሶሴሽን ነው፡፡

የኢትዮጵያ ቮሊቦል ፌዴሬሽን

የኢትዮጵያ ቮሊቦል ፌዴሬሽን በ1957 ዓ.ም የተቋቋመ ሲሆን ፌዴሬሽኑ ከተቋቋመ ጊዜ ጀምሮ የቮሊቮል ፌዴሬሽን በመላ ሀገሪቱ ውስጥ በመስፋፋት የታዳጊ ወጣቶች ስልጠና፣ የክለቦች ሻምፒዮና ውድድሮች፣ የኢትዮጵያ ሻምፒዮና ውድድሮችና የመላ ኢትዮጵያ ጨዋታዎችን ሲያካሂድ ቆይቷል፡፡

የኢትዮጵያ ፈረስ ስፖርት አሶሴሽን

የፈረስ ስፖርት አንድ የአገራችን ባህላዊ ስፖርት ሲሆን ለኢትዮጵያዊ የደስታው፣ የሀዘኑ፣ የጀግንነቱና የማንነቱ መታወቂያ ቀርጥ ነው፡፡ ዘመናዊ የፈረስ ስፖርት በኢትዮጵያ መዘውተር የጀመረው በዳግማዊ አጼ ምኒሊክ ዘመን መንግሥት ሲሆን ነው፡፡ ዘመናዊ የፈረስ ስፖርት ከጣሊያን ወረራ በፊት ተጀምሮ ጣሊያንም በኢትዮጵያ ውስጥ አምስት ዓመት በቆየበት ጊዜም ጭምር የውጪ ኮሚኒቲዎች የፈረስ ክለብን እያስተዳደሩ ስፖርቱ ሣይቋረጥ ይካሄድ ነበር፡፡ በ1933 ጠላት ተሸንፎ ሲለቅና ግ/ቀ/ኃይለ ሥላሴ አዲስ አበባ ሲመለሱ አብረዋቸው የመጡትን እንግሊዞች ዘመናዊ የፈረስ ስፖርቱን በኃላፊነት እንዲያቋቁሙና ኢትዮጵያውያን ፈረሰኞች እንዲያሰለጥኑ አድርገዋል፡፡

ከዘመናዊ የፈረስ ስፖርት ዓይነት ጥቂቶቹ የፈረስ ዝላይ ውድድር፣ የፈረጥ ሽርጥ ውድድር፣ የፈረስ ገና ውድድር፣ ድሬ ሳጅ ውድድር፣ ቮልቲንግ ውድድር ክሮስ ካንትሪ ውድድር ኢትዮጵያ በሀገር ውስጥና በውጪ አገር የምትሳተፍባቸው ውድድሮች ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ የፈረስ ስፖርት አሶሼሽን ስፖርቱን በሁሉም ክልሎች በተደራጀና በተቀናጀ ሁኔታ ለማስፋፋት መጠነ ሰፊ ስራዎችን በመስራት ላይ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን

የኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን በ1948 ዓ.ም የተቋቋመ ሲሆን ስፖርቱ በየደረጃው እየተስፋፋና ተወዳጅነት እያገኘ በመምጣቱ በሀገር ደረጃ የብሔራዊ ቡድን በማቋቋምና በ1954 ዓ.ም የአፍሪካ ዋንጫ ላይ በመሳተፍና አህጉር አቀፉንም ፌዴሬሽን ተቀላቅሏል፡፡ በሀገር ውስጥም ዓመታዊ ውድድሮችን፣ ኢንተርናሽናል ውድድሮችንና የወዳጅነት ውድድሮችን ከበርካታ ሀገሮች ጋር በማካሄድ ተሳትፎዋአ ከፍተኛ ልምድ በመቅሰም ስፖርቱ እንዲስፋፋ የበኩሉን አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ፌዴሬሽኑ በሁሉም የሀገሪቷ ክልሎችና ከተማ መስተዳድሮች ስፖርቱ በስፋት እየተዘወተረና እየተወደደ የመጣ ሲሆን   የኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽንም ከ1989 ዓ.ም ጀምሮ የታዳጊ ወጣቶች ፕሮጀክት በመዘርጋት በርካታ ተተኪ ወጣቶችን በማፍራት የታዳጊ ወጣቶች ውድደር፣ የክልሎች ውድድርና የክለቦች ውድድርና እያካሄደ ይገኛል፡፡

   የኢትዮጵያ ክብደት ማንሳት ፌዴሬሽን

ፌዴሬሽኑ በ1970 ዓ.ም የተቋቋመ ሲሆን የክብደትና ሰውነት መገንባት ስፖርትን ለማስፋፋትና ህዝባዊ መሠረት እንዲኖረው ከተቋቋመ ጀምሮ በርካታ የአሠልጣኝነትና የዳኝነት ኮርሶችን በመስጠት በርካታ ባለሙያዎችን አፍርቷል፡፡ ስፖርቱ በየክልሉ ታዋቂነት እንዲኖረው የክልል ፌዴሬሽኖችን     በማቋቋም ስፖርቱን የማስፋፋት ስራዎችን እየሰራ ይገኛል፡፡ ፌዴሬሽኑ በሁለት ዓመቱ የኢትዮጵያ ሻምፒዮና ውድድሮችንና የኢትዮጵያ መላ ጨዋታን በማካሄድ በክልሎች መካከል የእርስ በእርስ ፉክክር ልምድ ልውውጥ እንዲዳብርና እንዲጠናከር በማድረግ ላይ ሲሆን ምርጥ ስፖርተኞችን በማፍራት በብሔራዊ ደረጃ በማዘጋጀት በመላው አፍሪካ እና በአለም አቀፍ ደረጃ እንደወትሮው ሁሉ ለመሳተፍ ጥረቶች እያደረገ ነው፡፡

 የኢትዮጵያ ሞተር ስፖርት ፌዴሬሽን

በሀገራችን የሞተር ስፖርት በህብረተሰቡ ዘንድ እንዲዘወተርና እንዲወደድ ለማድረግ በመላው ሀገሪቱ ለማስፋፋትና ለማሳደግ ብሎም የተቋቋመበትን ዓላማ ከግብ ለማድረስ በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኝ ሲሆን በሀገር ውስጥ በሰፋፊ ከተሞች በአዲስ አበባ፣ በሀዋሣ፣ በባህር ዳር፣ በአዳማ የመኪና ውድድሮችን በማካሄድ ላይ ያለ ሲሆን በኦሮሚያ ክልል ለውድድር ተብለው በተሰሩ ቢስታ የገጠር መንገዶች ላይም ራሊ የመኪናና የሞተር ሳይክል ውድድሮችን ያካሂዳል፡፡

የኢትዮጵያ ካራቴ ፌዴሬሽን

የኢትዮጵያ የካራቴ ፌዴሬሽን እንደ ፌዴሬሽን በ1992 ዓ.ም የተቋቋመ ሲሆን የካራቴ ስፖርትን በኢትዮጵያ በማስፋፋት እየተደረገ ያለው ጥረት በተለያዩ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትና በተለያዩ ክልሎች የሥልጠና ፕሮጀክቶችን በመክፈትና በማሠልጠን ላይ ሲሆን በአሁኑ ሠዓት በሁለቱ የከተማ አስተዳደሮችና በዘጠኙም ክልሎች እየተዘወተረ ይገኛል፡፡ በቀጣይ በተለያዩ የውድድር መድረኮች ላይ ውጤታማ ለመሆን ጠንክሮ ለመሥራትም እቅድ ይዟል፡፡

የኢትዮጵያ ጅምናስቲክ ፌዴሬሽን

የኢትዮጵያ ጅምናስቲክ ፌዴሬሽን በ1973 ዓ.ም በሀገር ደረጃ የተቋቋመ ሲሆን በ1987 ዓ.ም የአለም አቀፍ ጅምናስቲክ ፌዴሬሽን በመሆን ግንኙነቱን ጀመረ፡፡ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ለጅምናስቲክ ስፖርት ውድድር ትኩረት በመስጠት ለስፖርት ወሣኝ የሆኑ ስልጠናዎችን በማካሄድ በሀገር ውስጥ ውድድሮች ላይ ከፍተኛ ተሳትፎ አድርጓል፡፡

የኢትዮጵያ ጅምናስቲክ ፌዴሬሽን ከኢንተርናሽናል ጅምናስቲክ ፌዴሬሽን ጋር በመተባበር ከሰባት በላይ የስፖርት አይነቶችን ይመራል፡፡ በሀገር ውስጥ ወደ አራት የሚሆኑ የስልጠና አይነቶችን በአሰልጣኝነትና በዳኝነት ዙሪያ ሲሠጥ፣ ከአምስት ያላነሱ የአሠልጣኝነት ስልጠናዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ በመስጠት ከሰባት በላይ የሚሆኑ የስፖርት አይነቶች ከአለም አቀፍ ፌዴሬሽን ጋር በመተባበር ይሠራል፡፡

የኢትዮጵያ ቴኒስ ፌዴሬሽን

የኢትዮጵያ ቴኒስ ፌዴሬሽን በ1966 ዓ.ም የተቋቋመ ሲሆን፣ በቴኒስ ስፖርት አንድ ተጫዋች በአለም አቀፍ ደረጃ አሸናፊና ተወዳዳሪ የሚሆንበት እድሜ ክልል በወጣትነት ዕድሜ ክልል ውስጥ በመሆኑ ውጤት ለማምጣት ፌዴሬሽኑ ከሰባት አመት እድሜ ጀምሮ ባሉ ታዳጊዎች ላይ ስራ መስራት ከጀመረ ሠንበትበት ብሏል፡፡

የኢትዮጵያ ወርልድ ቴኳንዶ ፌዴሬሽን

የኢትዮጵያ ወርልድ ቴኳንዶ በ1970ዎቹ ውስጥ በአገራችን የተቋቋመ ሲሆን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በወርልድ ቴኳንዶ ስፖርት የተሻለ አሠራር በመፍጠርና በስፖርት ፖሊሲ ላይ በተቀመጠው መሠረት ህብረተሠቡ በሚኖርበት፣ በሚማርበትና በሚሠራበት አካባቢ የስፖርቱን ጥቅም እንዲያውቅና እንዲሳተፍ በተደረገው እንቅስቃሴ በተለይ ስፖርቱ በወጣቱ ዘንድ የሚወደድ በመሆኑ በአሁኑ ጊዜ በሀገራችን በርካታ ወጣቶች በስፖርቱ እየተስፋፋ እና ተጠቃሚ እየሆኑ ይገኛሉ፡፡

የኢትዮጵያ ቦክስ ፌዴሬሽን

የኢትዮጵያ ቦክስ ፌዴሬሽን እ.ኤ.አ በ1962 የተመሠረተ ሲሆን አገራችን በቦክስ ስፖርት በኦሊምፒክ መሣተፍ የጀመረችው እ.ኤ.አ ከ1964 ቶክዮ ላይ በተደረገው ኦሊምፒክ እስከ 2008 በቻይና ቤጂንግ በተደረገው ኦሊምፒክ ድረስ ነው፡፡

ፌዴሬሽኑ በአገር ውስጥ የቦክስ ስፖርትን ለማስፋፋትና ለማሣደግ ብሎም በአለም አቀፍ እና በአህጉር አቀፍ ያለውን ተሳትፎ ለማሳደግና ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት ከጥር 2001 ዓ.ም ጀምሮ አዲስ የውድድር ስርዓት በመቅረጽ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ክለቦች ቦክስ ውድድር በሁሉም የአገሪቱ ክልል ዞኖች በሁለቱም ጾታ የክለቦች ሻንፒዮና በማካሄድ የሕብረተሠቡን ተሣትፎ ለማሣደግና ምርጥ ስፖርተኞችን ለመምረጥ የዙር ውድድሮች በማካሄድ ላይ ይገኛል፡፡

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን

በኢትዮጵያ የአትሌቲክስ ስፖርት መቼ እንደተጀመረ የተፃፉ መረጃዎች ለማግኘት ባይቻልም ከ 1980 ዓ.ም በፊት በትምህርት ቤቶችና በወታደራዊ ካምፖች ይዘወተር እንደነበር አንዳንድ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ቀስ በቀስ ስፖርቱ በመላ አገሪቱ በሕዝቡ ዘንድ ተዘውታሪ እየሆነ በመምጣቱ ስፖርቱን በበላይነት የሚመራ የኢትዮጵያ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን በ1941 ዓ.ም ተቋቋመ፡፡ በዚሁ ዓመት ፌዴሬሽኑ የዓለም አቀፍ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር (IAAF) አባል በመሆንም ተመዝግቧል፡፡  የኢትዮጵያ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ከተቋቋመ በኋላ ስፖርቱን በማሳደግና ክለቦችን በማቋቋም የተለያዩ ውድድሮችን ማካሄድ ጀመረ፡፡

የኢትዮጵያ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን በአለም አቀፍ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማኅበር አባልነት በተጨማሪ የአፍሪካ አትሌቲክስ ኮንፌዴሬሽን አባል ሲሆን በምሥራቅ አፍሪካ ዞን ደግሞ በአመራር ደረጃ በማገልገል የአትሌቲክስ ስፖርት በአገራችን ብቻ ሳይሆን በአፍሪካ ሀገሮችም እንዲስፋፋ ያላሠለሰ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ ፌዴሬሽኑ ስፖርቱን በኅብረተሠቡ ዘንድ ከማስፋፋት ባሻገር አለም አቀፍ ተወዳዳሪ አትሌቶች እና ተተኪዎችን አፍርቶ በአለም አቀፍ ውድድር መድረኮች በማሳተፍ ላይ ይገኛል፡፡

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን

ዘመናዊ ስፖርቶች ወደ ሀገራችን ሲገባ ቀደምት ሥፍራ ከሚይዙት ስፖርቶች መካከል አንዱ ሲሆን በፌዴሬሽን ደረጃ በ1936 ዓ.ም ተቋቋሟል፡፡ ስፖርቱ በ1945 ዓ.ም የዓለም አቀፍ ማህበር አባል፣ በ1949 ዓ.ም ደግሞ የአፍሪካ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አባል ሆኗል፡፡ በኢትዮጵያ ስለ ስፖርት አጀማመር ሲነሳ በመጀመሪያ የሚታወሰው ስፖርት ከመሆኑም በላይ ለሌሎች ስፖርቶች መሰረት የሆነው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከ31 ዓመት በኋላ በአፍሪካ ዋንጫ በመሳተፍ በህብረተሰቡ ዘንድ ከፍተኛ መነቃቃት በመፍጠር ላይ የሚገኝ ስፖርት ነው፡፡